በሐረሪ ክልል የሸዋል ዒድ በዓልን ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል “ሸዋል ዒድ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ ጀምሮ ለሚከበረው የሸዋል ዒድ በዓል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንደገለጹት፥ በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር የክልሉ መንግስት ሲያደርግ የቆየው ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው ሸዋል ዒድ በዓል ህብረ ብሔራዊነትን ሊያጎለብቱና የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ሊያስፋፉ በሚችሉ መሰናዶዎች እንደሚከበር ተናግረዋል።
በክብረ በዓሉም የሐረሪን ቱባ ባህልና እሴት የሚያስተዋውቅ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት የሚደረግበት መድረክ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
በክልሉ የሚገኙ ቅርሶች የሚታወቁበትና ይበልጥ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ለማድረግ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም አስታውቀዋል።
የሸዋል ዒድ በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና እንደሚሰጥም ጠቁመው፤ በበዓሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና አጎራባች ክልሎች የሚሳተፉበት የባህል ፌስቲቫልና ዓውደ ርዕይ ተዘጋጅቷልም ብለዋል።
“ሐረር ህያዊቷ ሙዚየም” የሚለው ሎጎ ወደ ስራ የሚገባበት የምርቃት ስነ-ስርዓትም ይካሄዳል።
በአሁኑ ወቅት የበዓሉ ታዳሚዎች ወደ ሐረሪ ክልል እየገቡ መሆኑን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡