Fana: At a Speed of Life!

ሠነድ አልባ ዜጎችን የመለየትና የጉዞ ሠነዶች በወቅቱ እንዲደርሳቸው የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጂቡቲ የሚኖሩ ሠነድ አልባ ዜጎችን በአግባቡ የመለየትና የጉዞ ሠነዶችን በወቅቱ እንዲደርሳቸው የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ ልዑክ በጂቡቲ የሚኖሩና ሀገሪቱን እንደመሸጋገሪያ በመጠቀም ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ሠነድ አልባ ዜጎች ያለባቸውን ችግር ለመቅረፍ ብሎም በኬላ ቁጥጥር ላይ ያለ ትብብርን ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሯል፡፡

በውይይቱም ኢትዮጵያውያን በአግባቡ በመለየትና ሠነዳቸውን በማጣራት የጉዞ ሠነድ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ሀገር የማስመለስ ሥራ ላይ ያለው ክፍተት እንዲስተካከልና ይህንንም ወጥ በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በውይይቱ ላይ እንዳሉት÷ ጂቡቲ የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር በመሆኗ ከዜግነት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንዲሠሩ አስገንዝበዋል፡፡

በድንበር አካባቢ የሚደረጉ ቁጥጥሮችም ጠበቅ ሊሉ እንደሚገባ መናገራቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የጂቡቲ ኃላፊ ታኒያ ፓሲፊኮ በበኩላቸው÷ ከፍልሰተኞች ሠነድና ወደ ሀገራቸው የማስመለስ ሥራ ጋር በተያያዘ በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው÷ ሠነድ አልባ ዜጎችን በአግባቡ የመለየትና የጉዞ ሠነዶችም በወቅቱ እንዲደርሳቸው የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

ከዜጎች ማጣራት እና ከድንበር ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍም ሥርዓቱን የማዘመንና ወቅቱን በሚመጥን አግባብ የማደራጀት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.