Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ምስጋኑ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱና የኢትዮጵያን የወጪ ምርቶችን እንዲገዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጠየቁ፡፡

ጃፓን በሚገኘው የኢትዮጵያ ሚሲዮን አዘጋጅነት በተካሄደው የኢትዮ-ጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ሴሚናር የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከኢትዮጵያ 15 እንዲሁም ከጃፓን ደግሞ 105 በአጠቃላይ 120 ኩባንያዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በወቅቱ እንዳሉት÷ መድረኩ ለዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ይረዳል።

ሀገራቱ የንግድ ልውውጥ ለማጠናከርና በኩባንያዎች መካከል ሽርክና ለመፍጠር ሴሚናሩ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉና የወጪ ምርቶችን እንዲገዙም ጠይቀዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያና በጃፓን መካካል ያለውን የንግድ ልውውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርአያስላሴ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ÷ በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አቅሞች፣ እድሎች፣ ማበረታቻዎችን እና ባለሀብቶችን ለመሳብ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ግንበታዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ-ጃፓን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሴሚናር በስኬት መጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ በጃፓን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና አምባሳደር ዳባ ደበሌ ናቸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.