Fana: At a Speed of Life!

ሐረሪዎች ያበረከቱት ቅርስና ዕሴት ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ሆኗል – አቶ ቀጀላ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐረሪዎች ያበረከቱት ቅርስና ዕሴት ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ሆኗል ሲሉ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ፡፡

በሐረሪዎች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የሸዋል ዒድ ዋዜማ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች መከበር ጀምሯል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፥ ሐረር የዳበረ ዕሴትና ባሕል ባለቤት ነች፤ በተለይ የሸዋል ዒድ በዓል ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ነው ብለዋል።

ሐረሪዎች ፍቅርና አብሮነትን ከቀደምቶቻቸው ተቀብለው ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፉ በኩል እየተወጡት ያለው ሚና የሚደነቅ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ያበረከቱት ቅርስና ዕሴትም ድንበር ተሻጋሪ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፥ ሐረር ትውፊታዊና ዕምነታዊ ባሕሎች የሚንፀባሩቁባት ከተማ መሆኗን ገልፀው፤ ፍቅርና አብሮነት ባሕሉ የሆነው የሐረር ሕዝብ በሸዋል ዒድ ዕለት ደምቆ የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሸዋል ዒድ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ መመዝገቡን አስታውሰው፤ በዓሉ ሁሉም የሚያከብረው መሆኑ ለመመዝገቡ ዋነኛ ምክንያት ነው ብለዋል።

አሁንም ክልሉ ለሚያደረገው እንቅስቃሴ የቱሪዝም ሚኒስቴር ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፥ ሐረር ሁለት ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከሀገራችን ከተሞች ቀዳሚ ነች፤ ይህም ለቱሪዝሙ ዘርፍ የጎላ ሚና አለው፤ ይህን ታሳቢ በማድረግም እንደ ክልል እድሎችን የማስፋት ስራ እየተከወነ ነው ብለዋል።

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.