Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ኬንያ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርን ከጎርፍ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ 2 ሪጂን የኢትዮ-ኬንያ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የደቡብ 2 ሪጂን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ፋይበር ኦፕቲክስ ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉብርሃን ሐዱሽ እንዳስታወቁት፥ በተካሄዱ የፍተሻ ስራዎች የተወሰኑ የመስመሩ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በመሆኑም ምሰሶዎቹ በጎርፍ ከመጎዳታቸው በፊት መከላከል የሚያስችሉ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማስተላለፊያ መስመሩ በሚያልፍበት የጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጎርፍ ስጋት የተጋረጠበትን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ከመውደቅ ለመከላከል የሚያስችል የአፈር መሸርሸር መከላከያና የጎርፍ ማስቀየሻ ግንብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

ምሰሶው ሲተከል ከወንዙ 35 ሜትር በላይ ርቀት የነበረው ቢሆንም በአካባቢው ከጥቅምት 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባጋጠመ ከፍተኛ ጎርፍ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከወንዙ ያለው ርቀት ከ3 እስከ 4 ሜትር ብቻ ነው ብለዋል፡፡

በአካባቢው ያለው አፈር ልል በመሆኑ ችግሩ አሁን ካለበት ቦታ ላይ በፍጥነት ሊደርስ እንደቻለ ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፥ በአካባቢው ዝናብ ቶሎ ባለማቋረጡ ምክንያት ችግሩን በወቅቱ መቅረፍ እንዳልተቻለም ነው የተናገሩት፡፡

መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ሥራ አስፈላጊው ጥናትና ዲዛይን ተሰርቶለት በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋ፡፡

በሥራው ላይም 87 ሜትር ርዝመትና 5 ሜትር ቁመት ያለው የአፈር መከላከያ ግንብ ሥራ በሪጂኑ አቅም እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

አሁን እየተከናወነ ካለው ሥራ በተጨማሪ በመስመሩ ላይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ተጨማሪ አራት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች መለየታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማም ችግሩ ሳይሰፋ ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ከኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.