Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ውጤታማ ድጋፍና ክትትል ማድረጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሁሉም ዞኖች ተሰማርተው ውጤታማ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ ማከናወናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ገለጹ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው፡፡

ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ በመድረኩ ላይ÷ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከመጋቢት ወር ጀምሮ በሁሉም ዞኖች ስምሪት በመውሰድ እስከ ታች ዘልቀው ድጋፍ እና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ገልጸዋል።

በዚህም የሕዝብና የመንግሥት ምልከታ እና ተግባቦት ምን እንደሚመስል በዝርዝር መፈተሹን፣ ችግር ያለባቸውን ቦታዎች በማወቅ ለማስተካከል ውጤታማ ስምሪት ተደርጓል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ስምሪቱ የሕዝቡን ፍላጎት በውል በመለየት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው መድረክ ላይም በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።

ከሰላም አኳያ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውም በቀረበው ጽሑፍ ተመላክቷል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ የፀጥታ መዋቅር እና አመራር ተቋቁሞ የሕዝብን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት እየተሠራ ስለመሆኑም ተገልጿል።

ከልማት እና መልካም አሥተዳደር አኳያም ጥሩ እንቅስቃሴ መኖሩ በጽሑፉ ተገልጿል።

ለአብነትም÷ የገቢ ግብር አሰባሰብ እንቅስቃሴ ወደተሟላ ሥራ መግባቱ፣ በግብርና ሥራዎች ላይ ርብርብ ለማድረግ ተነሳሽነት መፈጠሩ፣ የሥራ እድል ፈጠራ ግብረ ኃይል ሥራ እንዲጀምር መደረጉ፣ ትምህርት ባልጀመሩ አካባቢዎች ትምሕርት ቤቶች መከፈታቸው ተነስቷል።

በተጨማሪም የጤና ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ መሆኑን እና ሕዝብን በማያገለግሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ላይ ጠንካራ የተጠያቂነት ሥራ መዘርጋቱ ከልማት እና መልካም አሥተዳደር አኳያ በጥንካሬ ተነስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.