Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዋና መዳረሻ ሆናለች – አምባሳደር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዋና መዳረሻ ሆናለች ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮ-አሜሪካ ቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሂዷል፡፡

በፎረሙ በዓለም ባንክና በዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ስብሰባ የተገኘው በአቶ አህመድ ሺዴ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ተሳትፏል።

በተጨማሪም ወደ 150 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እና የአሜሪካ ባለሃብቶች በፎረሙ መሳተፋቸው ተነግሯል፡፡

ፎረሙ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሁም የዓየር ንብረት ሁኔታዎች ላይ ምክር ለማድረግ እድል የሰጠ እንደሆነም ተነግሮለታል፡፡

ለባለሀብቶችም ጠቃሚ የኔትወርክ መድረክ እንደነበርም አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ጠቁመዋል።

አክለውም፥ ኢትዮጵያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዋና መዳረሻ ሆናለች ያሉ ሲሆን፥ በአፍሪካ ተመራጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ደረጃ ላይ 5ኛ እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡

እንደ ጉግል፣ ሜታ፣ ዳታብሪክስ እና ፓላንቲር ካሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር በቅርብ ጊዜ የተደረጉ የቴክኖሎጂ ሽርክናዎች የእኛን ጋባዥ የንግድ ከባቢን ያመላክታል ሲሉም ነው የጠቆሙት፡፡

በአቪዬሽን፣ በአይቲ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና የሰው ሃይል ልማት እንደጨርቃጨርቅ፣ ማዕድን፣ ፋይናንስ እና ቴሌኮም ባሉ ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች እድገቶች ኢትዮጵያን ቀዳሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ያደርጋታል ሲሉም ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.