Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ አዳዲስ አሰራሮችን በመቀመር የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል -አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዳዲስ አሰራሮችን በመቀየስ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

አቶ እንዳሻው የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ያደረገውን ውይይት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ÷ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቢሮዎችን መክፈት፣ ሰባቱንም ማዕከላት ከህዝቡ ጋር ማስተዋወቅ፣ የህዝብ ውይይቶችን ማካሔድ እና ግብዓት የማሰባሰብ ሥራዎችን ተከናውነዋል ብለዋል።

የበጀት ዓመቱን የእቅድ ዝግጅት ማድረግ እና ፈጻሚዎችን የማብቃት እንዲሁም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የተከለሰ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የመከለስ ስራ በትኩረት ማከናወን መቻሉም አብራርተዋል።

በክልሉ ከ126 ሺህ በላይ ፈጻሚዎች እና ከ4 ሺ 700 በላይ አመራሮች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ለዓመቱ የተዘጋጀው እቅድ ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ሥራ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

በሁሉም ሴክተሮች የታቀዱ ተግባራትን ለማሳካት የሁሉም አመራር እና የባለሙያው ተሳትፎ ውጤታማ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡

ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ በችግሮች መሐል በማለፍ የተከናወኑ ተግባራትን በአብነት የጠቀሱት አቶ እንዳሻው÷ በሁሉም ስራዎች የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጎልበት የተጀመረው ጥረት ስኬታማ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም የክልሉ ሰራተኞች እና አመራሮች ለዓመቱ የታቀዱ ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የጋራ ተሳትፎ ማሳየታቸውን በመስተዳድር ም/ቤቱ እውቅና እንደተሰጠው ጠቅሰዋል፡፡

ለግብርና፣ለትምህርት፣ለጤና፣ለገቢ አሰባሰብ እና ለንግድ ስርዓት ውጤታማነት የሚረዱ አዳዲስ ሀሳቦችን እና የአሰራር ስልት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.