Fana: At a Speed of Life!

ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ወጥ አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ እንደሚያስፈልግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስገነዘበ፡፡

አገልግሎቱ “ሀገራዊ መግባባት እና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና” በሚል ርዕስ ለኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ከበደ ዴሲሳ በስልጠናው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ ወጥ የሆነ መረዳትና አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመሠረታቸው በመረዳት የሰላም ግንባታ ሂደቱን ለማፋጠን የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በሥልጠናው የመጀመሪያ ቀንም ‘የገዥ ትርክት ግንባታ እና የኮሙኒኬሽን ሚና’ በሚል ርዕስ የብልፅግና ፓርቲ ህዝብ እና አለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጻ አቅበዋል፡፡

ገዥ ትርክት የሀገር አንድነት መሠረት መሆኑን ያመላከቱት አቶ አዲሱ÷ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትርክቱን በመትከልና በማጽናት ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

የሥልጠናው ዓላማም የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፉን በሥልጠና በማገዝ ወቅታዊ፣ ትክክለኛ፣ የተናበበ እና የተቀናጀ መረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥና ሚዲያን በአጀንዳ ለመምራት ዐቅም ለመፍጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አሥተዳደሮች የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት፣ ከዞንና ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ 200 ለሚጠጉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ነው ስልጠናው እየተሰጠ የሚገኘው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.