የባቡር ሐዲድ ብረት በመስረቅ የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ነው – ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ በተዘረጋው የባቡር ሀዲድ ብረት ላይ ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የመልካ ጀብዱ ፖሊስ ጣቢያ አስታወቀ፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና ለጊዜው ያልተያዙ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ፖሊስ ገልጿል።
በሀሰሊሶ ክላስተር ገደንሳር ቀበሌ ቦሬ አካባቢ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ የቀድሞውን ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ የተዘረጋውን የባቡር ሀዲድ ብረት ፈትተው 47 ፍሬ በመኪና በመጫን ለመሰወር ሲሞክሩ አንድ ተጠርጣሪ ከነኤግዚቢቱ መያዙ ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ተሰርቆ በሌላ አካባቢ ተደብቆ የነበረ ከ300 ፍሬ በላይ የሀዲድ ብረት ከቦታው ላይ ተነቅሎ ለመጓጓዝ ሲዘጋጅ መያዙን የድሬዳዋ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
ፖሊስ ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ባደረገው ጥረትም ሁለተኛውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡