Fana: At a Speed of Life!

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር ከሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት በሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን አረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ለሚገኙ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ አጋርተዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበት ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በዓሉን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና አብሮ በማሳለፍ ሁላችንም የድርሻችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ብለዋል።

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሳሙኤል ታፈሰ፤ ማዕከሉ በበዓላት ወቅት ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራት ተግባር ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ማዕከሉ አሁን ላይ ለ700 አረጋውያን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ጤና ሚኒስቴር ሁሉ ሌሎችም ተመሳሳይ እገዛና ድጋፍ እንዲያደረጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሰንሻይን ፊላንትሮፊ ፋውንዴሽን ድጋፍ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተገነባው የአረጋውያን መጠለያና መጦሪያ ማዕከል በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.