Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ህዝብ ሰላም በማረጋገጥ መደበኛ ሥራውን እየመራ መሆኑን ተመልክተናል – የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ህዝብ በአብዛኛው ሰላሙን በማረጋገጥ ልማትና መደበኛ ስራውን እየመራ መሆኑን መመልከታቸውን የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

የፓርቲ አመራሮቹ ጎንደር ከተማ ሰላማዊ መሆኗን ያለምንም ስጋት ከተማዋን ተዘዋውረን በመጎብኘት አረጋግጠናል ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በጎንደር ከተማ ዘጠኝ ወራት የፓርቲውን የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አፈጻጸም ገምግመዋል።

የተለያዩ ክልሎች የፓርቲው አመራሮች እንዳሉት÷ ወደ ጎንደር ከመምጣታቸው አስቀድሞ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገቡ መረጃዎች የከተማዋን ገፅታ የማይመጥኑና አካባቢው ሰላም እንዳልሆነ የሚያስመስሉ ነበሩ።

ጎንደር አጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ ጊዜ ጀምሮ የከተማዋ ድባብ ፍጹም ሰላማዊና የህዝቡ እንቅስቃሴም መደበኛና ሞቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ሀሰተኛ መረጃና መሬት ላይ ያለው እውነታ ለየቅል መሆኑንን ያሳያል ነው ያሉት።

የክልሉና የከተማዋ አመራር፣ የፀጥታ ኃይሎች እና ህዝቡ የፅንፈኞችን እኩይ ተግባር በማክሸፍ ሰላምን ማስፈናቸውን በአካል ተገኝተን አረጋግጠናል ብለዋል።

በጎንደር ከተማ ማህበረሰቡ በንግድ፣ በአገልግሎትና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፤ በሩቅ የሚሰማው ግን ከዚህ ተቃራኒ እንደነበር አውስተዋል።

ስለ አማራ ክልል የሰላም ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገበውና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያየ ነው ያሉት አመራሮቹ፥ አካባቢው ሰላማዊ ህዝቡም የዕለት ተዕለት ህይወቱን እየመራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የከተማዋ ህዝብ እና አመራር በቆይታቸው ላደረጉላቸው ደማቅ እንግዳ ተቀባይነት አመስግነው፥ በቀጣይ ወደየክልላቸው ሲመለሱም የአማራ ክልል በአብዛኛው ሰላም እንደሆነ የግንዛቤ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.