Fana: At a Speed of Life!

 የፓኪስታን ባለሃብቶች በአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲፈጥሩ ኢትዮጵያ ሚናዋን ትወጣለች ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፓኪስታን ባለሃብቶች በአፍሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲፈጥሩ ኢትዮጵያ ሚናዋን እንደምትወጣ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ገለጹ።

በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፓኪስታን ፌዴራል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር የቢዝነስ ፎረም አካሂዷል፡፡

በፎረሙ ላይ አምባሳደር ጀማል በከር÷ የፓኪስታን ባለሃብቶች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባላቸው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስር ኢትዮጵያን እንደ መግቢያ በር መጠቀም እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡

የ2ኛው የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን ከፈረንጆቹ ግንቦት 26 እስከ 30 ባሉት ጊዜያት በ6ኛው የአዲስ ቻምበር የማኑፋክቸሪንግ እና ቴክኖሎጂ የንግድ ትርኢት ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

በፓኪስታን የሚገኙ ባለሀብቶች ከልዑካን ቡድኑ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ በማኑፋክቸሪንግ እና ንግድ ትርዒቱ ላይ በመሳተፍ ከአፍሪካ አምራቾች ጋር እንዲገናኙ መክረዋል።

የፓኪስታን የንግድ እና የኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳቂብ ፋያዝ በበኩላቸው÷ የፓኪስታን የንግድ ማህበረሰብ በአፍሪካ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ሰፊ አማራጭ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የፓኪስታን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ልዑክ በኢትዮጵያ በሚያደርገው ጉብኝት በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ንግድ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና የሚኖረው በመሆኑ በጉብኘት ላይ የምክር ቤቱ አባላት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የፓኪስታን የንግድ ልማት ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዙበይር ሞቲዋላ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ እምቅ የንግድ እና የልማት አማራጮችን በማሰስ የንግድ ትስስሩን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.