Fana: At a Speed of Life!

በግብርና ዘርፍ ያገኘነውን ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመድገም ትልቅ ትልም አለን-ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርና ዘርፍ ያገኘነውን ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመድገም ትልቅ ትልም አለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን በኦሮሚያ ክልል እና በሲሲኢሲሲ መካከል በተደረገ በገዳ የኢኮኖሚ ዞን የሉሜ ነፃ የንግድ ቀጠና ማልማት ስራ የመግባቢያ ስምምነት መርሃግብር አስጀምረዋል።

ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ የገዳ ኢንዱስትሪ ዞን የሀገራችን እና የቀጠናችን አቅም በመግለጥ ርዕያችንን ለማሳካት የሚረዳ ቁልፍ ተቋም ሆኖ ያገለግላል ብለዋል ።

የሉሜ ነፃ የንግድ ቀጠና በኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ሆኖ በምስረታው ብሎም ተግባራዊ ስራ በሚጀምርበት ወቅት ከድሬዳዋ በመቀጠል ሁለተኛው ነፃ የንግድ ቀጠና ይሆናልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም ነጻ የንግድ ቀጠናው ለኢኮኖሚ እድገት እና ልማት እድሎችን ያሰፋል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል።

በግብርና የተገኘው ስኬት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የመድገምን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም የፖሊሲ ድጋፍ ብሎም ለኢኮኖሚ ዞኑ ቀጣይ እንቅስቃሴ ጠንካራ የመሰረተ ልማት ስራ ሊከናወን እንደሚገባ አስምረውበታል።

ከአዲስ አበባ ከተማ በስተምሥራቅ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ተቋም ኤክስፖርትን ለማሳደግ፣ የንግድ እና ሎጂስቲክስ ማዕከል የመመስረት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ፣ የኢንዱስትሪ የንግድ ኢንቨስትመንት እና የከተማ ልማት ስራዎችን የማበልፀግ አላማ ያነገበ መሆኑ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.