Fana: At a Speed of Life!

የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን የፍልሰት ምጣኔ ለመግታትና ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) ጋር ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የአይኦኤም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቢባቱ ዋንፎል ተፈራርመዋል።

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ በርካታ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለማት በህገ ወጥ መንገድ ስለሚሸጋገሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ለእንግልትና ለተባባሰ ችግር ይዳረጋሉ ብለዋል።

መንግስት በዚህ ረገድ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለማቃለል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

ለዚህም በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የአምስት ዓመት እቅድ አንዱና ዋነኛው ሲሆን÷ እቅዱን በአግባቡ ለመፈጸም የአጋር አካላት ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ከአይኦኤም ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ቀደም ሲል በቅንጅት የሚሰሩ ተግባራትን ለማጠናከርና ለቀጣዩ የ5 ዓመት እቅድ አተገባበር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

አቢባቱ ዋኔ-ፎል በበኩላቸው÷ በፍልሰትና የስደተኞች ደህንነት ማረጋገጥ ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በርብርብ በመስራት ጉዳቱን መግታትና ማስቆም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ችግሩን ለማቃለል የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ድርጅታቸው የሚያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.