Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ሰብዓዊነት ድንበር እንደሌለው አሳይቷል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ሰብዓዊነት ድንበር እንደሌለው ያሳየ ነው ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ቢሮ የተመሰረተበት አምስተኛ አመት ተከብሯል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የፋውንዴሽኑ ዋና ዳይሬክተር ዋንግ ጀን ባደረጉት ንግግር÷ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ፕሮጀክት እንዳለው ገልጸዋል።

ፕሮጄክቶቹ በዋናነት ድህነትን በማጥፋት፣ ረሃብን ዜሮ በማድረግ፣ የንጹህ ውሃ ተደራሽነትን በማስፋትና ጤናማ ማህበረሰብን በመፍጠር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ኮንስለር ሚስትር ያንግ ይሃንግ÷ ቻይና በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።

የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክቶች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን መደገፉን እንደሚቀጥል ገልጸው÷ የፋውንዴሽኑ ፕሮጀክቶች የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክር አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካ ዘርፍ ለአመታት የዘለቀ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል።

የቻይና ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ሰብዓዊነት ድንበር እንደሌለው ያሳየ ፕሮጄክት መሆኑን ጠቅሰው፤ ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመሆን ሲያበረክት ለቆየው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

በዚህ ፕሮጀክት  እስከ  ፈረንጆቹ 2023 መጨረሻ 10  ነጥብ 54 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ 320 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።

 

በተያያዘም የቻይና ኢንተርፕራይዞች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡

 

 

 

 

 

በሃይማኖት ኢያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.