Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የአስተዳደር ርክክብ ተካሄደ

 

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የአስተዳደር ርክክብ መርሀ ግብር ተካሄደ።

በመርሀ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት ንግግር ቻይና በዘረጋችው ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የተገነባው የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መንገድ መሠረተ ልማት ዘርፈ ብዙ ውጤቶች አስመዝግቧል ብለዋል።

የባቡር መንገድ መሰረተ ልማቱ ለኢትዮጵያ አማራጭ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት በመሆን የንግድ ሥርዓቱን ማሳለጡንም ገልጸዋል።

በግብርና፣ ንግድና ትራንስፖርት፣ ቱሪዝምና ኮሙኒኬሽን ዘርፎች ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመልክቷል።

ቻይና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በሚል በዘረጋችው መርሃ ግብር በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ፋይናንስ ግብዓት አቅርቦት ረገድ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማዕከሏ አድርጋ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።

በዚህም በፈረንጆች 2023 መገባደጃ ድረስ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው 400 የቻይና የግንባታ እና የማምረቻ ዘርፍ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.