በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በእስያ ሀገራት ዘንድ ግልጽነት እንዲፈጠር ተሰርቷል- በኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በእስያ ሀገራት ዘንድ ግልጽነት እንዲፈጠር መሰራቱን በኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
በኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር አድማሱ ጸጋዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ የእስያ አባል ሀገራት ኢትዮጵያ በቀጠናው እየፈጠረች ያለውን ትስስር ለመደገፍ ዝግጁነት ማሳየት ጀምረዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት ያሳየችው ሁለንተናዊ ለውጥ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኝ አስችሏታልም ብለዋል።
ለውጡ በእስያ ሀገራት ዘንድ አድናቆት እንደተቸረው ያነሱት አምባሳደሩ፥ የእስያ ሀገራት በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ፈቃደኝነታቸውን እንዲያሳዩ ምክንያት ሆኗልም ነው ያሉት።
በተሰሩ ስራዎች ጥሩ ምላሽ መገኘቱን ጠቅሰው፥ በአጭር ጊዜ የመጣውን ተስፋ ሰጭ ውጤት ለማሳደግ ተጨማሪ አሰራሮችን በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ ላይ የተሰራው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ኢትዮጵያ እውቅናን እንድታገኝ አድርጓል ያሉት አምባሳደሩ፥ በተለይ ግድቡ በጋራ ለምቶ በጋራ ለመበልጸግ የሚያስችል መሆኑን በእስያ አባል ሀገራት እውቅና እንዲያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህ ስራም ቀድሞ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የነበራቸውን አሉታዊ አመለካከት መቀየር የቻለ መሆኑን አንስተዋል።
በግድቡ ዙሪያ ቀድሞ በተሰራ ፕሮፖጋንዳ ሀገራቱ ኢትዮጵያ የሌላውን መብት በመጋፋትና በመጉዳት የራሷን ተጠቃሚነት ብቻ ለማረጋገጥ እየሰራች ነው የሚል እሳቤ እንደነበር ጠቁመው፥ አሁን ላይ በተሰራ ስራ ይህ አስተሳሰብ ተቀይሯልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የእስያ አባል ሀገራት ጽህፈት ቤት መቀመጫ በሆነችው ጃካርታ ኤምባሲዋን ከከፈተች በኋላ ከፍተኛ የገጽታ ግንባታ መፍጠር መቻሉ ተመላክቷል።
በሃይለኢየሱስ ስዩም