Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የ2012 በጀት ዓመት የስራ ግምገማ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2012 በጀት ዓመት የስራ ግምገማ እያካሄደ ይገኛል።

በትናንትናው ዕለት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከኢኮኖሚ አኳያ ያከናወኗቸውን ተግባራት ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

በዛሬው ዕለትም በማኅበራዊው ዘርፍ የተሠማሩት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ካወጧቸው መሥፈርቶች አንጻር ክንውናቸውን እያቀረቡ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

ምክር ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት የታቀዱ ዋና ዋና ስራዎችን በመገምገም ለቀጣይ ግብዓቶችን መሰነቅ የሚያስችለውን ግምገማ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገልጸዋል።

የበጀት ዓመቱ ማጠቃለያና የቀጣዩ ዓመት የዕቅድ ዝግጅት ጊዜ በመሆኑ ለዚሁ መነሻ የሚሆን የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ ንጉሱ ከዚሁ የተቀዳ የአምስት ዓመት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት መደረጉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ምክር ቤቱ ትናንት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በዘርፍ በመክፈል የኢኮኖሚ ዘርፍ ተብለው በተለዩ ዘጠኝ መስሪያ ቤቶች አፈጻጸም ግምገማውን ጀምሯል።

ግምገማው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ዋና ዋና ዕቅዶች አፈጻጸም፣ የገጠሟቸው ችግሮች፣ መልካም ተሞክሮዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤቱ ዛሬም የ11 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ተጠሪ ተቋማትን የስራ አፈጻጸም ገምግሞ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አቶ ንጉሱ ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.