መድረክ እና አብን ለ 2012ቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 7፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ 2012ቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መድረክ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሀገሪቱ ህገ መንግስት ይደነግጋል።
በዚህ መሰረትም በተያዘው ዓመት እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳለው አሁን ሀገሪቱን እየመራው የሚገኘው መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይስተዋላል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መድረክ እና የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን (አብን) በበኩላቸው ፥ለ2012ቱ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ የአረና ትግራይ፣ የሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ እና የሲዳማ አርነት ንቅናቄን አቅፎ የሚንቀሳቀሰው መድረክ ሊቀ መንበር ፕሮፈሰር መረራ ጉዲና፥ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ መካሄድ አለበት ብለው ከሚያምኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው ለመወዳዳር የሚያስችሉ በቂ አጀንዳዎች እንዳሉት የሚገልፁት ፕሮፌስር መረራ፥ ለ2012 ምርጫ እጩዎችን የማዘጋጀት፣ አዳዲስ ቢሮዎችን የመክፈትና ነባሮቹን የማጠናከር ስራ በማከናውን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
መድረክ በፌዴራልና በክልል ፓርላማ ስልጣን ለመካፈል አሊያም በመሪነት ደረጃ ለማሸነፍ የሚያስችለውን ወንበር ለማግኝት ይወዳዳራል ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፥ ለዚህም በምርጫው ተፎካክሮ ያስቀመጠውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ አባላቱን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና መስጠቱን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ፕሮግራሞቹን የማስተዋወቅ እና ህዝብ የማወያየት ስራ በማከናውን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
በ2012 ምርጫም በአራት ክልሎች በርካታ እጩዎችን በማቅረብ ለመወዳደር የሚያስችለውን ዝግጀት በተጠናከረ መልኩ እያከናውነ እንደሚገኝም አክለዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፥
ለአማራ ህዝብ ምን አዲስ ነገር እናመጣለን? ለኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካ ምን እናበረክታለን? የሚለውን ጨምሮ ፓርቲው ለምርጫ 2012 የሚያደርጋቸውን በርካታ ዝግጅቶች አያገባደደ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው በቅርቡ ለ2012ቱ ሀገራዊ ምርጫ የመወዳዳሪያ ፖሊሲዎቹንና ፕሮግራሞቹን የመገናኛ ብዙሃንን በመጥራት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም አንስተዋል።
በምርጫው የሚወዳደሩ የፖርቲው እጩዎችን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደሳለኝ፥አዲሱን የምርጫ ህግ ለአባላቱ የማስተማር ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወንም መንግስት በሀገሪቱ ያለውን ሰላም በዘላቂነት ማረጋጋት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ለሀገራዊ ምርጫው የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን በተገቢው ጊዜ እና ሰዓት ማከናወን የሚጠበቅበት መሆኑን አመላክተዋል።
ሁለቱ አካላት ከሚያደርጉት ቅድመ ዝግጅት በተጓዳኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ገቢራዊ እንዲሆን አባሎቻቸውን ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በበላይ ተስፋዬ