የፌደራል ፖሊስ አዲስ የደንብ ልብስ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አዲስ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ ባካሄደው ስነ ስርዓት ላይ ነው አዲስ የተቀየረውን የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ ይፋ ያደረገው።
በስነ ስርዓቱ ላይም የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰውን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፥ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስን መቀየር እንደ ሀገር የተጀመረው ሪፎርም አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
የፖሊስ ሰራዊት ለህዝብ ልብና ፍላጎት የቀረበ ብሎም ዘመን ተሻጋሪ ሊሆን ይገባል ሲዩም ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው፥ የፌዴራል ፖሊስን የደንብ ልብስን በአዲስ መቀየር ያስፈለገበት ምክንያት ልብሱ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ላይ በመቆየቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ለደንብ ልብሱ መቀየር አሁን ያለው የደንብ ልብስ በቀላሉ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ በስነ ምግባር ችግር የተባበሩ ፖሊሶች ልብሱን ለብሰው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በዚህም የደንብ ልብሱን በመልበስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና ዝርፊያዎች መበራከታቸውን ነው ያስታወቁት።
በሌላ በኩል የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ወደ ሥራ እንዲገቡ የታሰበ መሆኑንም መግለፃቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።