ጠ/ሚ ዶ/ር አብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኤርትራ ኤምባሲ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።
ሀምሌ 19 መናፈሻ አካባቢ ለሚገነባው ለዚህ ኤምባሲ ሁለቱ መሪዎች የመሰረት ድንጋዩን በጋራ አስቀምጠዋል።
በዚህም ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት የኤምባሲ መገንቢያ ቦታው ለኤርትራ ህዝብና መንግስት የተሰጠ ስጦታ መሆኑን አብስረዋል።
የኤምባሲው መገንባት የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የበለጠ መሰረት የሚያስይዝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በዚህ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት ወቅት ሀገራቱ በርካታ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸው አቅም እንዳላቸው ተመልክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንንም ለመጠቀም ተወያይተናል ብለዋል።
የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ከድህነት ለማስወጣት ያለ መታከት እንሰራለንም ነው ያሉት።
የፈረንጆቹ 2020 ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ህዝቦች ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ የብልፅግና መጀመሪያ ዓመት ይሆናልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ብልፅግና አብሮ መስራት በኢትዮጵያ በኩል ሙሉ ዝግጁነት እንዳለም ጠቁመዋል።
የአሁኑ የሁለት ቀናት ጉብኝቴ የሁለት ወራት ቆይታን ያህል ነው የተሰማኝ ያሉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፥ ጉብኝቱ በበርካታ በድንገቴ አስደሳች ሁነቶች የተሞሉ መሆኑን ነው የገለፁት።
በአልአዛር ታደለ