በግድቡ ዙሪያ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጠናክሩ ናቸው – የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጠናክሩ እንጂ ስጋትን የሚፈጥሩ አለመሆናቸውን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ፡፡
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ በኢትዮጵያውያን ሀብት እና እውቀት እየተገነባ ያለውን የህዳሴ ግድብ የመጨረስ እና የመጠቀም ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በራስ አቅም ማደግ እንደሚችሉ የሚያሳየው ፕሮጀክት ከፍፃሜ እንዲደርስም ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ ድጋፉን እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉትም የዶናልድ የትራምፕ ንግግር ቀጠናውን ካለመረዳታቸው የመነጨ ነው፡፡
በስልጣን ላይ እያሉ በሉዓላዊ ሀገር ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ሀገራትን ጦር ለማማዘዝ መቀስቀሳቸውም በታሪክ ተወቃሽ እንደሚያደርጋቸው ጠቁመዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ በበኩላቸው አስተያየቱ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋ ያላትን ኢትዮጵያ ከጀመረችው ድህነትን የማሸነፍ ጉዞ አያስቆማትም ነው ያሉት።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ግድቡ ከፍፃሜ ደርሶ ከ65 በመቶ በላይ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ብርሃን መስጠት ይችል ዘንድ የተጀመረው ህዝባዊ ድጋፍ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም በሁለት ተርባይኖች የሚጀመረው ሀይል የማመንጨት ሙከራ ህዝባዊ ድጋፉን ይበልጥ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በፋሲካው ታደሰ