ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ስርዓትን ለመገንባት እንደሚሰራ የብልፅግና ፓርቲ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አካታች የኢኮኖሚ ስርዓትን ለመገንባት እንደሚሰራ የብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።
ለዚህም የግሉን ዘርፍና ሀገራዊ ባለሃብቱን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ ፓርቲው ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ከሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር በወቅታዊ የብልፅግና ፓርቲ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል
በውይይቱ ላይም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይም ከ1 ዓመት ከ8 ወር በፊት ሀገራዊ ለውጡ ሲመጣ መነሻ ሀሳቡ ምን ነበር፤ ከለውጡ በኋላ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችስ ምን ምን ናቸው በሚለው ላይ የመነሻ ሀሳብ ቀርቧል።
እንዲሁምብልፅግና ፓርቲ ምን አይነት የኢኮኖሚ አማራጮችን ይዞ መጥቷል የሚለው ላይም የመነሻ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በዚህም ሀገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ አሳሪ ህጎች መነሳታቸውን፣ ከግብር ጋር በተያያዘ ዘጠኝ ህጎች መሻሻላቸውን፣ ውዝፍ ግብር ላለባቸው የእፎይታ ጊዜ መሰጠቱ እና የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያግዙ 26 ህጎች ላይም ማሻሻያዎች መደረጉ ተነስቷል።
ተሳታፊዎቹም ከግብር ካር በተያያዘ በርካታ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም ቢሆን ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ከሌሎች አሰራሮች ጋር ቀሪ ስራዎች እንዳሉ አንስተዋል።
ተሳታፊዎቹ የሰላም ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ያነሱት ሲሆን ሰላም ከሌለ ንግድ የለም፤ ስለዚህ ሀገራዊ ሰላም ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
መንግስት ፍትሃዊ እና ህጋዊ አሰራርን ማስፈን እንዲሁም የአሰራር ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በርካታ የማሻሻያ ስራዎችን መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በለይኩን ዓለም