ሀገራት አዲሱን 2020 ዓመት በተለያዩ ክብረ በዓላት ተቀብለዋል
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአለም ሀገራት የፈረንጆቹ 2020 አዲስ ዓመትን በደማቅ የርችት ትእይንቶች እና በተለያዩ የበዓል ድግሶች ተቀብለዋል።
ኒውዝላንድ፣ አውስትራሊያ እና በርካታ ትናንሽ የፓስፊክ ደሴት ሀገራት አዲሱን ዓመት 2020ን በመቀበል ቀዳሚ ሀገራት ሲሆኑ፥ ተከትለው ሌሎች የእስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አውሮፓ ሀገራት አዲስ አመታቸውን ተቀብለዋል።
ፓሪስ፣ በርሊን፣ ማድሪድ እና አቴንስን ጨምሮ የአውሮፓ ከተሞች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ታላላቅ የርችት ተኩስ ትእይንቶች አስተናግደዋል።
የብሪታኒያዋ ለንደን የክብረ በዓሉ አካል የሆነው ትልቅ የጎዳና ላይ ፓርቲ የተደረገባት ሲሆን፥ 12 ሺህ የሚሆኑ ርችቶች ተተኩሰዋል።
ባከር እና ሆውላንድ የተባሉና ሰው የማይኖርባቸው ደሴቶች ደግሞ ከዓለም መጨረሻ በመሆን አዲሱን ዓመት ይቀበላሉ ተብሏል።