Fana: At a Speed of Life!

ሜ/ጄ ገብረ መድህን ፈቃዴን ጨምሮ 7 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የጦርነት ቅስቀሳና የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባሰቡ ነበር-የፌዴራል ፖሊስ

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሜጀር ጄነራል ገብረ መድህን ፈቃዴን ጨምሮ በሰባት  ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ በተደረገ ምርመራ በአዲስ አባባና በተለያዩ አካባቢዎች በተጀመረው ጦርነት በትግራይ ሰራዊት አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ በሚል ቅስቀሳ ሲያደርጉንና የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባሰቡ እንደነበር መረጃ ማገኘቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

በተለይም 1ኛ ተጠርጣሪ ሜጀር ጄኔራል ገብረ መድህን ፈቃዴ (ወዲ ነጮ) በመንግስት በጀት ለህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን ሰዎችን  እየመለመለ ለሁለት ወር የስራ ፍቃድ በመስጠት አበል በመክፈል ወደ ትግራይ በድብቅ በመላክ ለቡድኑ ድጋፍ ሲያደረግ ነበር ሲል መርማሪ ፖሊስ በተሰጠኝ የምርመራ ጊዜ መረጃ ሰብስቤ አለው በማለት አብራርቷል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ በሁለተኛ መዝገብ በቀረቡ የመከላከያ አካዳሚ ኮሌጅ አመራር የነበሩ እነ ብርጋዴር ጄነራል አሊጋዝ ገብሬን ጨምሮ አራት መኮንንችም  1 ለ 20 በሚል ተደራጅተው ወንጀሉን ለመፈጸም ሲሰሩ እንደነበር ባገኘሁት ማስረጃ አርጋግጫለው ሲልም ለችሎቱ አብራርቷል።

ዛሬ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርፍ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለሶስተኛ ጊዜ የቀረቡት ከፍተኛ ጦር መኮንንኖች ከጠበቆቻቸው ጋር ተገኝተዋል።

በቀዳሚነት ችሎቱ የተመለከተው ሜጀር ጄነራል ገብረ መድህን ፈቃዴን ጨምሮ የ7 ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጉዳይ ሲሆን ፤ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ አባላት ከዚህ በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ  ያከናወነውን ምርመራ አዳምጧል።

መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው  ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አባባና በተለያዩ አካባቢዎች በተጀመረው ጦርነት በትግራይ ሰራዊት አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ በሚል ቅስቀሳ ሲያደርጉንና የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባሰቡ እንደነበር መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።

ከተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት በርካታ የገንዘብ መጠን ያለው የተለያዩ የባንክ ሂሳባቸውን በብርበራ አግኝቻለው አሁን ለተፈጸመው ወንጀልም በገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ አንደነበርም ማስረጃ ሰብስቤያለው ያለው መርማሪ ፖሊስ ፤

አጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አባባ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ መገናኛ ሬዲዮ ኔትዎርክን በማቋረጥ በሰራዊቱ ላይ ጥቃትና ዝርፊያ እንዲፈጸም ማድረጋቸወን የሚገልጽ ማሰረጃ አግኝቻለሁ ሲል አስታውቋል።

መርማሪ ፖሊስ ቀሪ የቴክኒክ ምርመራን ጨምሮ ሰፊ ስራን የሚጠይቅ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ ያሰፈልገኛል ሲል ችሎቱን ጠይቃል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ምርመራው በተናጠልና በየደረጃ ተሳትፏቸው አልቀረበም ፤ለተጨማሪ ምርመራ እና ግብረ አበር ለመያዝ በሚል ተጨማሪ ጊዜ ሊጠየቅ አይገባም ሲሉ መቃወሚያ አሰምተዋል።

የዋስትና ጥያቄም ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪዎቹም ፤የባንክ ሂሳባቸው መታገዱን ገልጸው እግዱ እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል።

የጤና እክል ያለብን ስላለን ህክምና መመርመሪ ይግባልን ሲሉም የመብት ጥያቄ ለችሎቱ አቅርበዋል።

መርማሪ ፖሊስም በታሰሩበት ቦታ 5 ሜትር ላይ የህክምና ኪሊኒክ አለ እዛ መታከም ይችላሉ ነገር ግን ባሉበት የህክምና መሳሪያ ማስገባት በሌሎች እስረኞች ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ሲል ስጋቱን ጠቅሷል።

የባንክ ሂሳባቸው እግድ በአቃቢህግ መታገዱን ባለፈው ቀጠሮ ገልጸናል የሚመለከተው እሱ ነው ያለው መርማሪ ፖሊስ የጠፋው የበርካታ ሰዎች ህይወት ነው ንብረትም ወድሟል ምርመራው ሰፊ በመሆኑ ቅዳሜና እሁድ ሳይቀር እየሰራን ነው በዚህ ልክ ሊታይ ይገባል ብሏል።

ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ ትዛዝ ለመስጠት በይደር ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

 

በሌላ በኩል በሁለተኛ መዝገብ በቀረቡት የመከላከያ አካዳሚ ኮሌጅ ከፍተኛ አመራሮች  እነ ብርጋዴር ጄነራል አሊጋዝ ገብሬን  ጨምሮ አራት መኮንንችም የምርመራ መዝገብን ችሎቱ ተመልክቷል።

መርማሪ ፖሊስም በተሰጠኝ ተጨማሪ ጊዜ በሁለተኛ መዝገብ በቀረቡ የመከላከያ አካዳሚ ኮሌጅ አመራር የነበሩ እነ ብርጋዴር ጄነራል አሊጋዝ ገብሬ ጨምሮ አራት መኮንንችም 1 ለ 20 በሚል ተደራጅተው ወንጀሉን ለመፈጸም ሲሰሩ እንደነበር ባገኘሁት ማስረጃ አረጋግጫለው ሲልም ለችሎቱ አብራርቷል።

በተጨማሪም በተለያዩ ድረ ገጾች የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃ ሲያቀብሉ ነበር ለዚህም ባደረኩት ምርመራ ማስረጃ አግኝቻለው ብሏል።

ቀረኝ ያላቸውን ምርመራዎች ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ነው ያለው።

ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የልጆቻቸን መማሪያ ኮምፒዩተር ለምርመራ ተወስዷል ሊመለስ ይገባል ሲሉ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የሚመራው ችሎቱ ለተጨማሪ ምርመራ  ለፖሊስ 12 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።

ችሎቱ የሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ጉዳይ ተመልክታል።

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል

https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.