መደበኛ ያልሆነ የኤርትራ ስደተኞች እንቅስቃሴ ደህንነታቸው ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 2፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከስደተኛ ጣቢያ በመነሳት የሚደረግ መደበኛ ያልሆነ የኤርትራ ስደተኞች እንቅስቃሴ ደህንነታቸው ላይ እና በሚደረግላቸው እንክብካቤ ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ አሳሰበ።
የመረጃ ማጣሪያ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን የመጡ 1 ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኑን አስታውቋል።
እነዚህ ስደተኞችም በ26 የስደተኞች ጣቢያዎች እና የስደተኛ ጣቢያ ባልሆኑ ስፍራዎች እየተስተናገዱ እንደሚገኝ የመረጃ ማጣሪያው ገልጿል።
በመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊው ጥበቃ ፣ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እያቀረበ ይገኛል ተብሏል።
በተመሳሳይ ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጭ ስደተኞች በፈለጉት የኢትዮጵያ አካባቢ መኖር እንዲችሉ የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ መስጠቱን አስታውሷል።
ነገር ግን ከመጠላያ ጣቢያ ውጭ መኖር የሚፈልጉ ስደተኞች አስፈላጊውን ህጋዊ ሂደት ማለፍ እንደሚገባቸው ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ ያሳሰበው።
በአሁን ወቅት 200 ሺህ የሚጠጉ የኤርትራ ስደተኞች በኢትዮጵያ የሚገኙ ሲሆን አብዛኛዎቹ በትግራይ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ይገኛሉ ተብሏል።
በቅርቡ የተጠናቀቃው በትግራይ የተወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ በመጠለያ ጣቢያዎችም እና ከመጠለያ ጣቢያ ለሚኖሩ የኤርትራ ስደተኞች ቅጥተኛ ስጋት አይደለም ነው የተባለው።
ሆኖም በተሳሳተ መረጃ አማካኝነት በማይ አይኒ እና አዲ ሐሪሽ የስደተኛ ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ መንቀሳቀሳቸው ተጠቁሟል።
መደበኛ ያልሆነው የስደተኞች እንቅስቃሴ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ፣ክብራቸውን ለማስጠበቅ ፣ በቅንጅት ድጋፍ እና ከለላ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል ተብሏል።
መንግስት ለስደተኞቹ የህይወት አድን አገልግሎት ለማቅረብ እና በግንባር ቀደምትነት ምላሽ ለሚሰጡ አካላት ደህንነቱ የተጠበቀ አከባቢ ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የተገለፀው።
በዚህም የምግብ ድጋፎች ወደ እነዚህ የስደተኞች ጣቢያዎች እየተሰራጩ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች በፌዴራል መንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉ በመሆኑ የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ናቸው ተብሏል።
ስለሆነም መንግስት ስደተኞቹ አገልግሎቶች ወደ ሚያገኙባቸው በተለይ በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ወደ ሚኖሩባቸው የስደተኞች ጣቢያ እንደሚመልስ አስታውቋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን