ኢራን የዩክሬንን አውሮፕላን በስህተት መታ መጣሏ ቁጣን ቀስቅሷል
አበባ፣ ጥር 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራን የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን በስህተት መታ መጣሏ የሀገሬውን ዜጎች ክፉኛ አስቆጥቷል።
የኢራን ባለስልጣናት 176 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረን የዩክሬን አውሮፕላን ከቀናት ማስተባበል በኋላ በስህተት ተመቶ መውደቁን በትናንትናው ዕለት ማመናቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ድርጊቱን በመቃወም ቴህራን አደባባይ ወጥተዋል።
በዚህም የተፈተጸመውን ይቅር የማይባል ስህተት በማውገዝ የኢራን ከፍተኛ አመራሮች ሃላፊነታቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
የጸጥታ ሃይሎችም ተቃዋሚዎችን ለመበተን የአስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው በዘገባው ተመላክቷል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃዋሚዎች የተፈጸመውን ስህተት ለመኮነን አደባባይ መውጣታቸው የሚበረታ ሃሳብ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በተያያዘ ዜና ተቃውሞን ተከትሎ የኢራን ጸጥታ ሃይሎች በሀገሪቱ የብሪታንያን አምባሳደር በቁጥጥር ስራ ማዋላቸው ተሰምቷል።
አምባሳደሩ በቁጥጥር ስር የዋሉትም በቴህራን የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ አነሳስተዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑ ተገልጿል።
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፥ኢራን በሀገሯ የሚገኘውን የብሪታንያ አምባሳደር ያለምንም ማብራሪያ በቁጥጥር ስር ማዋሏ ዓለማዊ ህግን የጣሰ ተግባር መሆኑን አስታውቋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ