የገቢዎች ሚኒስቴር በታህሳስ ወር 18 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ሰበሰበ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር በታህሳስ ወር 18 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በወሩ 18 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከእቅድ በላይ 18 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጿል።
አፈጻጸሙ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ22 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ ወይም የ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ልዩነት አሳይቷል ነው ያለው።
በወሩ ከሃገር ውስጥ ገቢ 8 ነጥብ 59 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከቀረጥና ግብር 9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰቡንም አስታውቋል።
አፈፃፀሙ ጥሩ ቢሆንም በቅርንጫፎች መካከል ያለውን የአሰባሰብ ልዩነት በመቅረፍ የተሻለ ገቢ ለመሰብስብ መስራት ይገባል መባሉን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።