የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥምቀት በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ በድምቀት ተከብሮ ዋለ።
በመላ ሀገሪቱ ትናንት ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ በመውረድ በዚያው ማደራቸው ይታወቃል።
ዛሬ ማለዳ በዓሉ ታቦታቱ ባደሩባቸው ጥምቀተ ባህር በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል።
በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የእምነቱ አባቶች እና መሪዎች እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት ነው በድምቀት የተከበረው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የጥምቀት በዓል ቤተክርስቲያኗ፣ መንግስት እና ህዝበ ክርስቲያኑ ባደረጉት ጥረት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ወካይ ቅርስነት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በመመዝገቡ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስርዓቱን ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣም የአደራ ብለዋል በመልዕክታቸው።
በመልዕክታቸው “እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው እጅግ ቀላል ፣ ዋጋ የማያስከፍል ፤ ጠቃሚ ነገር ነው እሱም ፍቅር ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እርሱ እንደወደደን እኛም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ይህን አዟል፤ ይህ ትዕዛዝም የህሊና ቁርጠኝነት እንጅ ሌላ እያስከፍልም ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በጃን ሜዳ የጥምቀት በዓል ሲከበር ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም የኢትዮጵያ ብቻ በተለይ የኦርቶዶክሳዊውን ሀብት የነበረው የጥምቀት በዓል ዘንድሮ የዓለም ሀብት በመሆኑ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የዓለም ሀብት የሆነውን ይህን በዓል መላ ኢትዮጵያውያን እናከብረዋለንን፤ እናሳድገዋለን፤ ለዓለም ህዝብም እናስተዋውቀዋለን ለዚህም ሃላፊነት እንወስዳልን ነው ያሉት።
ጥምቀት ዝቅ ማለትን ነው ያስተማረን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ሀገራችን እና ህዝባንን ዝቅ ብለን በማገልገል ሀገር እና ህዝብ ከፍ እንዲሉ ማድረግ እንደሚገባውም አንስተዋል።
አሁን ላይ ታቦታት ካደሩበት ጥምቀተ ባህር ወደ አድባራቶቻቸው ተሸኝተው በሰላም ገብተዋል።