በየመን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 111 ደርሷል
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በየመን ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት በወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ በተፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 111 ደርሷል።
የሚሳኤል ጥቃቱ የተፈጸመው ማሬብ አካባቢ በሚገኘው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ወታደሮች መስጂድ ውስጥ ጸሎት እያደረሱ በነበሩበት ወቅት መሆኑን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ይህም በየመን ከአምስት ዓመት በፊት በተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ከተፈጸሙት አሰቃቂ ጥቃቶች አንዱ መሆኑ በዘገባው ተመላክቷል።
መንግስት ለተፈጸመው ጥቃት የሃውቲ አማጺያንን ተጠያቂ ሲያደርግ፥ አማጺያኑ በበኩላቸው ለተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነት ከመውሰድ ተቆጥበዋል።
ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የየመኑ ፕሬዚዳንት አብደራቡህ ማንሱር ሃዲ፥የተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነት የጎደለው የሽብርተኞች ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቃቱ የሃውቲ አማጺያን ለየመን ሰላም ምንም አይነት ፍላጎት ብሎም ተነሳሽነት የሌላቸው መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው።
በሳኡዲ ጥምር ጦር በሚደገፉ የየመን መንግስት ታማኝ ወታደሮች እና በሃውቲ አማጺያን መካከል የሚደረገው ጦርነት በሀገሪቱ በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል።
በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ ባለፈም 11 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች የዕለት ተዕለት ምግባቸውን ለማግኘት የሚቸገሩ ሲሆን፥ 240 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ለአስከፊ ረሃብ መዳረጋቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
ምንጭ፥ቢቢሲ