Fana: At a Speed of Life!

የእናቶችን ጡት የማጥባት ጥሩ ተሞክሮ ማጠናከር የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 28፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የእናቶችን ጡት የማጥባት ጥሩ ተሞክሮ እንዲጠናከር ለማስቻል ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
ዓለም አቀፉ ጡት የማጥባት ሳምንት “ጡት ማጥባትን መጠበቅ፣ የጋራ ሃላፊነት!!” በሚል መሪ ሃሳብ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።
ጤና ሚኒስቴር እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ማጥባት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ በተገቢው መልኩ እንዲከናወን የሚያስችሉ እድሎችን ለማመቻቸት የሚያስችል ስምምነት ከአጋር አካላት ጋር ተፈራርሟል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም እንደተናገሩት÷ የኢትዮጵያ እናቶች ከጥንት ጀምሮ ጥሩ የሚባል ጡት የማጥባት ልምድና ባሕል አላቸው።
በኢትዮጵያ 97 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ያሳድጋሉም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ህጻናት ክብደታቸው ከሚጠበቀው በታች ሲሆን÷ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ከ6 ሚሊየን በላይ ህጻናት የቀነጨሩ ናቸው።
ከ1ሚሊየን በላይ ህጻናት ደግሞ የቀጨጩ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በስምምነቱ መሰረት እናቶች ከመውለዳቸው በፊት ጡት ለማጥባት የሚያስችላቸውን የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲያዳብሩና የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ይሆናል።
በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉና የሚያጠቡ እናቶች የሚደገፉበትና በምግብ እጥረት ምክንያት ልጆቻቸውን ማጥባት እንዳያቋርጡ ማገዝንም ስምምነቱ እንደሚያካትት የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስለጣን የምግብ ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር በትረ ጌታሁን÷ እናቶች ለልጆቻቸው የታሸጉ የወተት ምርቶችን ከማጠጣት ይልቅ ጡታቸውን እንዲያጠቡ መክረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.