Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ ረጅሙ ዕፅ ማዘዋወሪያ ዋሻ ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ ረጅሙን የዕፅ ማዘዋወሪያ ዋሻ ማግኘታቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ዋሻው አሜሪካን ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት ድንበር በኩል ዕፅ አዘዋዋሪዎች ይጠቀሙበት እንደነበረም ገልጸዋል።

1 ሺህ 313 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ የሜክሲኮዋን ቲጁዋና ከአሜሪካዋ ሳንዲያጎ ጋር የሚያገናኝ ነው ተብሏል።

በውስጡ አሳንሰር (ሊፍት)፣ የባቡር ሀዲድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ኤሌክትሪክ ሃይል መሸከም የሚችል መስመር እና አየር መቆጣጣሪያ መሳሪያ እንዳለውም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

የሜክሲኮ ባለስልጣናት ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ የዋሻውን መግቢያ ያገኙት ሲሆን፥ አሜሪካ የዋሻውን አጠቃላይ ይዞታ የሚያመላክት ካርታ ካዘጋጀች በኋላ በትናንትናው እለት ይፋ ሆኗል።

ዋሻው በተገኘበት ጊዜ ምንም አይነት አደንዛዥ ዕፅ ያልተገኘ ሲሆን፥ እስካሁን ከዋሻው ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪ ቡድን መኖር አለመኖሩም አልተገለጸም።

ይሁን እንጅ ትልቁ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን የሆነው ሲናሎዋ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ ተነግሯል።

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.