የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የህግ ባለሙያዎች ጠየቁ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ጣቢያችን ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያዎች ገለጹ።
ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ውብሽት ግርማ እና መልካሙ ኡጎ ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መንግስት የዜጎችን መብት እንዲያስከብር ሊስራ እንደሚገባ አንስተዋል።
የህግ ባለሙያዎቹ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሆነ አሁን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መበራከታቸውን ይገልጻሉ።
የኮሚሽኑ ነጻና ገልተኛ አለመሆን እንዲሁም የአቅም ችግሩን አለመፍታቱ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለማስቆም አስቸጋሪ አድርጎበታልም ነው ያሉት።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ማርሸት ታደሰ በበኩላቸው፥ እንደ ሃገር ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ላይ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት መስራት ይገባል ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ደግሞ የተቋቋመለትን አላማ ማስፈጸም የሚያስችል ቁመና እንደሌለው አምኗል።
ኮሚሽኑ ያሉበትን ችግሮች ለይቶ ተቋማዊ የማሻሻያ ስራ መጀመሩንም ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ የማሻሻያ ስራው የኮሚሽኑን የማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻል፣ የኮሚሽነሮችን ምርጫ ገለልተኛ ማድረግ እና የክልል ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ማደራጀትን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በመንግስታቱ ድርጅት የጸደቀውን ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ብቃት እና ገለልተኛነት መመዘኛ መስፈርት እንደማያሟላ ይነገራል።
አወል አበራ