ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካምነቱንና ፍቅሩን የሚገልጽበት በዓል ነው – አባገዳዎች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካምነቱንና ፍቅሩን የሚገልጽበት በዓል መሆኑን አባገዳዎች ገልጹ።
“ኢሬቻ የአንድነት፣የፍቅር፣የይቅር ባይነትና የመተባበር በዓል ነው” ያሉት አባገዳዎቹ ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩም ለትውልዱ እንዲተላለፍ እየሰራን ነው ብለዋል።
የሁምበና በሬንቶ አባገዳ ጉግሣ ኢብሣ፤ በየዓመቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የሰላም ተምሳሌት በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካምነቱንና ፍቅሩን የሚገልጽበት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሬቻ አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ እና ይቅር ባይነት የሚሰበክበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢሬቻ ትውፊቱን ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ መከበር አለበት ያሉት አባገዳ ጉግሣ፤ በሚከበርበት ስፍራ ላይ የፖለቲካም ሆነ ከአከባበሩ ያፈነገጡ አስተሳሰቦች መንፀባረቅ አይችሉም ብለዋል።
በዓሉ ከማህበራዊ ጠቀሜታው ባሻገር በቱሪዝም ልማት የኢኮኖሚ አጋዥ በመሆኑ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ነው ያሉት።
የቱለማ አባገዳ ቦኮና ጩቃላ በበኩላቸው የኢሬቻ በዓል የሰላም ተምሣሌት በመሆኑ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሁሉም የጋራ ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢሬቻ ክብረ በዓል ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና መተባበር የሚሰበክበት በመሆኑ የኢትዮጵያን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር ልናከብረው ይገባል ብለዋል።
የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያንን የወንድማማችነት፣ አንድነት እና ፍቅር አጉልቶ የሚያሣይ በመሆኑ ሁሉም ብሄር ብሔረሰቦች በእለቱ ተገኝተው እንዲያከብሩትም ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበረው ኢሬቻ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡
የክረምት ወራት አልፎ ጸደይ ሲመጣ የሚከበረው “ኢሬቻ ብራ” የሚባል ሲሆን በዓሉ በውሃማ ሥፍራዎች ስርአቱን ጠብቆ ይከበራል።
ሌላኛው በበልግ ወቅት የሚከበረው “ኢሬቻ አርፋሳ” የተባለው አከባበር በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በከፍታ ቦታዎች ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት እንደሆነ ይነገራል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!