22 አካባቢ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 22 አካባቢ ትናንት ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለፁ።
ምክትል ከንቲባው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በተከሰተው ችግር የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን በማንሳት በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልፀዋል፤ ለሟች ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝተዋል።
“እነዚህን ወጣቶች ለማጣት ያበቁንን በየትኛውም ወገን ያሉ የጥፋቱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን” ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የሃይማኖት ተቋማት በተለይም ከይዞታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ሲመልስ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ በመንግሥት እና በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ጥቂት አጥፊዎች ምክንያት ያልታሰበ ድርጊት መፈጸሙን ነው ያስታወቁት።
ምንም እንኳን ቦታው ህጋዊ ባይሆንም በምሽት እንዲፈርስ ትእዛዝ መተላለፉ ልክ አልነበረም ያሉት ምክትል ከንቲባው፥ ትእዛዙን ያስተላለፈውን አካልም ለህግ እናቀርባለን ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ ድርጊቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና መንግስትን የማይወክል ነው ያሉት ኢንጅነር ታከለ፥ በቀጣይም ጉዳዩን ፖሊስ እየመረመረው እንደሆነ ገልፀዋል።
መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት በጋራ እና በመተሳሰብ እየሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት ይህ እኩይ ድርጊት መፈጸሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊሸረሽረው አይችልም ብልዋል።
በትእግስት ስለሺ እና ይስማው አደራው
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevisio