በቱርክ በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 170 ሰዎች ተጎድተዋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቱርክ ኢስታንቡል በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።
አውሮፕላኑ በኢስታንቡል አውሮፕላን ማረፊያ በማረፍ ላይ እያለ ከማኮብኮቢያው ተንሸራቶ በመውጣቱ አደጋው ደርሷል።
በዚህ ሳቢያም አውሮፕላኑ ሶስት ቦታዎች ላይ መሰባበሩ ነው የተገለፀው።
የፔገሰስ አየር መንገድ ጄት የሆነው አውሮፕላን 171 ሰዎችን እና 6 የበረራ አባላትን ይዞ ነበር ከቱርኳ ኢዝሚር በመነሳት ኢስታንቡል ያቀናው።
ቦይንግ 737 የሆነው አውሮፕላን አደጋው በደረሰበት ሰዓት ከፍተኛ ዝናብ እየጣለ እንደነበር ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በአደጋው የ3 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ170 በላይ ሰዎች ላይ ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ማጋጠሙን ነው የአካባቢው ባለስልጣናት ያስታወቁት።
አብዛኛዎቹ መንገደኞች የቱርክ ዜጎች ሲሆኑ፥ ከ12 ሀገራት የተውጣጡ የሌሎች ሀገራት ዜጎች እና የተወሰኑ ህፃናትም በአውሮፕላኑ ውስጥ ሳይኖሩ እንደማይቀር ነው የተገለፀው።
አደጋውን ተከትሎም የአውሮፕላን ማረፊያው ለተወሰኑ ሰዓታት ተዘግቶ በአደጋው ዙሪያ ምርመራ እየተደረገ ነው።
ምንጭ፦ ቢቢሲ