Fana: At a Speed of Life!

የህወሓትን ገመና የሚገልጥ ሁሉ ሰለባ የሚሆንበት ተቋም

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አሉታዊ ጫና ለመፍጠር የጸጥታ ምክር ቤቱ ተደጋጋሚ ስብሰባ አድርጓል።

በስብሰባዎቹ የተለየ ፍላጎት ያላቸው አገሮች የኢትዮጵያን መንግስት ለመወንጀል ሃጢያተኛ አድርገው ሲያቀርቡ፤ የኢትዮጵያን እውነት የሚገነዘቡ አገሮች ደግሞ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኢትዮጵያ መተው እንደሚገባ በመግለጽ አላግባብና በህገ ወጥ መንግድ የሚደረገውን ጫና አውግዘዋል፡፡

ያም ሆኖ ግን ተመድ ፀጥታው ምክር ቤትና አንዳንድ ምዕራባውያን፥ አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በመሸፈን መንግስትን ከመወንጀል ወደ ኋላ አላሉም።

መንግስት የውጭ ኃይሎች በተለይም በሰብዓዊ ድጋፍ ስም በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ቢያስገነዝብ፣ ቢያሳስብና ከአገር ቢያሰናብትም ጣልቃ የመግባት ዝንባሌው እየጨመረ መጥቷል።

በተለይም የተመድ ሰባት ሰራተኞች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸው የድርጅቱን ዋና ጸሐፊ ጨምሮ ያስደነገጣቸውና ያልጠበቁት በመሆኑ ጫናቸውን ለማበርታትና በሃሰት ኢትዮጵያን ለመወንጀል የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ አድርጓቸዋል።

ከሰሞኑ የታየው የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ሃላፊ የሰጡትን ቃለ-መጠይቅ ተከትሎ በአስተዳደራዊ እረፍት ስም ከኢትዮጵያ እንዲመለሱ መጠራታቸው የዚህ ማሳያ ነው።

ሃላፊዋ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የአሸባሪውን ህወሓት ትክክለኛ ገጽታ አሳይተዋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሃላፊዋ ማውሪን አቺንግ ከኢትዮጵያ መጠራታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው የኤ ኤፍ ፒ ዘገባ አመላክቷል።

የዚህ ውሳኔ ዋና መነሻው÷ ሃላፊዋ የኢትዮጵያን እውነት በመያዝ የተለያየ ጽሁፍ በማውጣት እየሞገተ ለሚገኘው ጸሐፊ ጄፍ ፒርስ ቃለ መጠይቅ በመስጠታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

በቃለ መጠይቁ የኢትዮጵያን እውነት አጉልተው በማውጣት የአሸባሪውን ህወሓት ትክክለኛ ገጽታ በአደባባይ አጋልጠዋል።

ቡድኑ እጅግ የቆሸሸ ድርጊት የሚፈጽምና በጭካኔ የተሞላ መሆኑንም ይፋ አድርገዋል።

ለአብነትም ከዚህ ቀደም ቡድኑ ከሳዑዲ አረቢያ ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ የትግራይ አካባቢ ተወላጆች ወደ ርዋንዳ እንዲላኩ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ይህ የቡድኑን ገመና የማውጣት ድርጊታቸው ደግሞ ኢትዮጵያን በሐሰት እየወነጀሉ ለሚገኙ ሃይሎች የሚዋጥ አልሆነም።

የስደተኞች ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አንቶንዮ ቪቶሪኖ፥ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ሃላፊ አቺንግ አስተያየት ተቋሙን የማይወክል መሆኑን በመግለጽ÷ የድርጅታቸውን መርህና እሴት የጣሰ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ይህንን የዋና ዳይሬክተሩን አቋም የኤጀንሲው የቀጣናው ሃላፊ ሞሐመድ አብዲከርም አጠናክረውታል።

“ለማንኛውም አካል ሳንወግን ገለልተኛ በመሆን ስራችንን እንሰራለን” በማለት ቢገልጹም÷ የተፈጸመው ድርጊት ግን ይህንን አያረጋግጥም።

የአሸባሪውን ህወሓት ገመና የሚገልጥ ሁሉ ሰለባ መሆኑን የሚያሳይ ውሳኔ እያሳለፉ ለመርህና ለእሴት እንገዛለን፤ ገለልተኛ ሆነን እናገለግላለን ማለት ያስተዛዝባል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.