በራችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ክፍት ነው – ቻይና
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሯ እንደማይዘጋ፣ ይልቁንም የበለጠ ክፍት እንደሚሆን አስታወቀች፡፡
የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ ጂንፒንግ÷ ቻይና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሯ ሁልጊዜም ክፍት እንደሆነ በ2ኛው የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ ዘላቂ የትራንስፖርት ኮንፈረንስ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ÷በወረርሽኙ ምክንያት በክፍለ ዘመናችን አይተን የማናውቃቸው ጉልህ ለውጦች ቢከሰቱም የዓለም እድገት እንዲሁም እየዘመነ የመጣው ዓለም አቀፋዊ የትራንስፖርት ትብብር ይለመልማል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በመሠረተ ልማት ትስስር ፣ ባልተገደበ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም በሥልጣኔዎች መካከል በሚደረጉ ሁለንተናዊ ግንኙነቶች አዲስ ምዕራፍ እንጽፋለን ነው ያሉት – ቺ ጂንፒንግ፡፡
ቺ – አክለውም ትራንስፖርት የኢኮኖሚ ደም ስር ነው ብለው÷ በሥልጣኔዎች መካከል ትስስር እንዲቀጥልና ዓለም እንደ አንድ መንደር እንድትቀራረብ የሚያስችል ዘርፍ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ቺ – በንግግራቸው ÷ የትራንስፖርቱ ዘርፍ እያደገ መምጣቱን ታሪክ አጣቅሰው አንስተዋል፤ በዘመናዊው ዓለምም የትራንስፖርቱ ዘርፍ እድገት ለኢኮኖሚ ትስስር እና ለህዝቦች ግንኙነት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የዘገበው ሲጂቲ ኤን ነው፡፡
በዓለማየሁ ገረመው