Fana: At a Speed of Life!

የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ፡፡

በዛሬው እለት ካስመረቁት መካከል ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ በተከታታይ እና በክረምት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 293 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል 4 ሺህ 804 ወንዶች ሲሆኑ፥ 2 ሺህ 489 ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡

በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የክብር እንግዶች የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ፥ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ እንዲሁም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት “መጭው ዘመን ለኢትዮጵያ የተስፋ ጊዜና የብልጽግና ዘመን እንዲሆን ከልዩነት ይልቅ አንድነትን መደማመጥና መከባበር እናስቀድም ዘንድ ትልቁ የቤት ስራ እናንተ ላይ መጣሉን ልትገነዘቡ ይገባል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኋላ ቀርነት፣ ከድህነት ለማላቀቅ በእድገትና ብልጽግና ለማራመድ ትምህርትን በጥራትና በስፋት ማዳረስ ለነገ የማይባል በመሆኑ ለትምህርት ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም ስራ ፈጣሪ ሆኖና ሩቅ አስቦ ለሃገራዊ ልማትና ብልጽግና የሚተጋ ዜጋን ማፍራት ከሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ይህን ታላቅ ራዕይ ሰንቀው ከሚጓዙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መሰረቱን ያደረገውነ የህዝብን ችግር መፍታትን ቀዳሚ አላማው ያደረገው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በእስካሁኑ ሂደት ለሃገር የሚበቁ ድንቅ ባለሙያዎችን እያስመረቀ አለኝታ እንዲሆኑ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በተመሳሳይ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው 525 ወንድና 432 ሴት በአጠቃላይ 957 ተማሪዎችን በአራት ኮሌጆችና በ21 የትምህርት መስኮች ነው ያስመረቀው፡፡

በተያያዘ ዜናም የወራቤ እና ጂንካ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የምትህርት መስኮች ያስመረቋቸውን ተማሪዎች አስመርቀዋል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው 854 ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ፥ ከዚህ ውስጥ 501 ወንድ እና 353 ሴቶች ናቸው፡፡

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ 629 ወንዶች እና 503 ሴት በድምሩ 1 ሺህ 132 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ እና ወራቤ የኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያስመረቁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

በዘቢብ ተክላይ ፤ ተጨማሪ መረጃ ከአብመድ እና ኢብኮ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.