አቶ ገዱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርን ተቀብለው አነጋገሩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋችው ዛሬ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑትን ማይክል ራይነር በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ሁለቱ ወገኖች በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
በተጨማሪም ከሚቀጥለው ሰኞ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ለ3 ቀናት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ስለሚያደርጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ አምባሳደር ማይክል ራይነር ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በቆይታቸው ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አስታውቋል።
በተጨማሪም በቀጠናዊ ጉዳችዮች ላይ ሀገራቱ ያላቸውን የጋራ ጥረትን ይመለከታሉም ብሏል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision