በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 14 ክላሽ ጠብመንጃ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢሉ አባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 14 ክላሽኮቭ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ገለፀ።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ታረቀኝ አሰፋ እንደገለፁት፥ የጦር መሳሪያው
የተያዘው በሚኒባስ ተሽከርካሪ ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ነው።
መሳሪያዎቹ ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት ተኩል አካባቢ በቡሬ ከተማ በተደረገው ፍተሻ በተሽከርካሪው ውስጠኛው አካል በላሜራ በተበየደ ቦታ ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል።
የሚኒባሱ አሽከርካሪ ለጊዜው መሰወሩን ገልፀው ሌሎች በውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች ግን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
አሽከርካሪውን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ኮማንደሩ፥ በቁጥጥር ስር በዋሉት ግለሰቦች ላይ ማጣራት እንደሚካሄድ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አካባቢው በተደጋጋሚ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲደረግ የሚያዝበት በመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑንም ኮማንደር ታረቀኝ ገልፀዋል።
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።