ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ በደቡብ ሱዳን የአንድነት መንግስት በመመስረቱ ደስታቸውን ገለፁ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች የአንድነት መንግስት ለመመስረት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለፁ።
በደቡብ ሱዳን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና የአማጺ ቡድን መሪ ሆነው የቆዩት ሪካ ማቻር ብሄራዊ የአንድነት መንግስት መስርተዋል።
በተመሰረተው የአንድነት መንግስት መሰረትም ሳልቫ ኪር የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፥ ሪክ ማቻር ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የሽግግር መንግስት ለመመስረት በመብቃታቸው የደስታ መግለጫቸውን ልከውላቸዋል።
ስኬቱም ለደቡብ ሱዳን የማእዘን ድንጋይ መሆኑንም በመልዕክታቸው አንስተዋል።
ድርድሩን ሲመራ ለነበረው ኢጋድም ውጤቱ ትልቅ እርካታን እንደሚፈጥርም ነው ያመለከቱት።
እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ህዝብም ሆነ ለሽግግር መንግስቱ ባስፈለገ ሰዓት ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።