በበልግ ወቅት የነበረው የአየር ጠባይ ትንበያ የተከሰተው ድርቅ በዜጎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር አስችሏል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበልግ ወቅት የነበረው የአየር ጠባይ ትንበያ በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ድርቅ በዜጎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ መቋቋም ማስቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለፁ።
የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ግምገማና የመጪው የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ይፋ የሚደረግበት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በመክፈቻው ላይ እንደገለፁት÷ የበልግ ወቅት የአየር ሁኔታ ትንበያ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቋቋም አቅም ለመገንባት ከማስቻሉም ባለፈ ሊደርስ የነበረውን አደጋ ማስቀረት ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት 6 ወራት የነበረው ድርቅ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንስቃሴዎች ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸው፥ ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ጠባይ ትንበያ ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ አበረታች ውጤት መኖሩንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢኒስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው÷ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴክተሮች ተለይተው በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ በመጪው ክረምት ትክክለኛ የአየር ንብረት ትንበያና መረጃ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ዘንድ እንዲደርስና የታሰበው ውጤት እንዲመጣ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።