ኢትዮጵያውያን በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የአመራርነት ቦታ እንዲይዙ ብዙ መሠራት አለበት- ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የአመራር ቦታ እንዲይዙ ብዙ መሠራት አለበት ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ አዲስ የተሾሙትን የአፍሪካ ሕብረት ልማት ድርጅት- አውዳ-ኔፓድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ ቶማስ ጋር ተወያይተዋል።
ስራ አስፈጻሚዋ ናርዶስ ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት በመብቃታቸውና የመጀመሪያ ሴት አመራር በመሆናቸው እንደ አገር የተሰማቸውን ኩራትና ደስታ ጠቅሰው÷ ያለንበት ወቅት በርካታ ፈተናዎችና ቀውሶች ያሉበት በመሆኑ ድርጅቱ ሚናውን እንዲወጣ ተገቢውን አመራር እንደሚሰጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የአመራር ቦታ እንዲይዙ ብዙ መሠራት አለበትም ብለዋል።
አውዳ-ኔፓድ 55 አገራትን የያዘ በዓለም ላይ ብቸኛ የልማት ድርጅት መሆኑን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአውዳ-ኔፓድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ናርዶስ በቀለ ባለፈው ጥር ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው የሕብረቱ ጉባኤ መሾማቸው ይታወሳል።