Fana: At a Speed of Life!

ስፖርታዊ ጨዋነትን በመጣስ ሁከት የሚፈጥሩ ደጋፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ 

አዲስ አበባ፣ ታኀሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፖርታዊ ጨዋነትን በመጣስ ያልተገባ ሁከት የሚፈጥሩ ደጋፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከሊግ ካንፓኒ፣ ከከተማው የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች፣ ከብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች እና ከመላው የስፖርት ቤተሰቦች ጋር በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በላይ ደጀን በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ስፖርቱን የማይወክሉ አንዳንድ ደጋፊዎች በስታዲየም ውስጥ የሚፈጥሩትን ሁከት በጋራ መከላከል ይገባል።

በሁሉም የስፖርት ዘርፍ በጋራ በመስራት ለሁለንተናዊ የስፖርት እድገትና ልማት መረባረብ እንደሚገባ ገልጸው፤ ስፖርቱን የማይወክሉ አካላት የጨዋታ ሜዳዎችን የሁከትና ብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት መከላከል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው÷ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለስፖርታዊ ጨዋነት እድገት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የእግርኳስ ደጋፊዎችም እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎችና የስፖርቱ ቤተሰቦች ስፖርታዊ ጨዋነት አስፈላጊ መሆኑ ጠቅሰው÷ እግር ኳስ የሰላም ምንጭ እንጂ  የግጭት ምክንያት ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ስፖርታዊ ጨዋነትን በመጣስ ያልተገባ ሁከት የሚፍጥሩ ደጋፊዎችን በመነጥል ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ መናገራቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.