Fana: At a Speed of Life!

ሀገር እንድትበልጽግና ሰላም እንዲረጋገጥ የወል ትርክቶችን መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር እንድትበልጽግና ሰላም እንዲረጋገጥ ከነጠላ ትርክት በመውጣት የወል ትርክቶችን በመገንባት አካታች የሆነ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገልጹ።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሄደ።

በውይይቱ ላይ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ ይገዙ ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች የኑሮ ውድነትን መከላከል፣ የህግ የበላይነት ማስከበር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ በትኩረት መስራት፣ ወጣቱን ማወያያት፣ ሰላምን ማጽናት፣ ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት፣ ሌብነት እና የመሬት ወረራን መከላከል ላይ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እንድትበልጽግና የሀገር ሰላም እንዲረጋገጥ ከነጠላ ትርክት በመውጣት የወል ትርክቶችን በመገንባት አካታች የሆነ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በጽንፈኝነት የትኛውንም የህዝብ ጥያቄ መመለስ እንደማይቻል ገልጸው፤ ነፍጥ አንግበው ጥያቄቸውን በኃይል ለማስመለስ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው ታቅበው በውይይትና በሃሳብ የበላይነት ብቻ እንዲታገሉ ጠይቀዋል።

የሀይማኖት አባቶችም “ሰላም” እንዲረጋገጥ ሚናቸውን እንዲወጡም አብዱ ሁሴን አመላክተዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ ግዙፍ እና አካታች ፓርቲ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገር ለመገንባት ፓርቲው እየሰራ ያለውን ስራ በመደገፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኑሮ ውድነት ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ችግር መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት በቂ ምርት ማምረትና ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.