Fana: At a Speed of Life!

በዕፅ ዝውውር የተያዘን የውጭ ዜጋ አስመልጠዋል የተባሉ የፖሊስ አባላት በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮኬይን ዕፅ ዝውውር የተያዘ የውጭ ሀገር ዜጋን አስመልጠዋል የተባሉ የፖሊስ አባላት በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።

ተከሳሾች በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥራ ላይ ተመድበው ሲሰሩ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ባሌማና ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሞገስ እንዲሁም የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም አቅርቦት የነበረው ክስ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) ሀ እና (2) መተላለፍ የሚል ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ እንዳመላከተው፤ ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ35 ላይ የብራዚል ዜግነት ያለውን ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የሚባል 4ኛ ተከሳሽ ከብራዚል ሳኦፓሎ ተነስቶ ትራንዚት በማድረግ ወደ ጆሃንስበርግ ለመሄድ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ “ሴንትራል ጌም” ተብሎ በሚጠራው የፍተሻ ጣቢያ ላይ በተደረገበት ፍተሻ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከተከለ 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ በሻንጣው ውስጥ ይዞ ተገኝቷል።

በወቅቱ 1ኛ ተከሳሽ ከሌሎች የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ሠራተኞች ጋር በመሆን ቆሞ የተያዘውን ዕፅ ካስቆጠረ በኋላ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን 4ኛ ተከሳሽ የሆነውን የውጭ ዜጋ ከእነ ዕፁ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አደንዛዥ ዕፅ መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የፀረ ፈንጅና አደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር መምሪያ ለማስረከብ በሚል ዕፁንና ግለሰቡን አሳድረው በነጋታው ታኅሣሥ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሠዓት ከ10 ላይ 1ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ግለሰቡን ከእነ ዕፁ ጭነው ወደ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ መውሰዳቸውን ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ አስፍሯል።

ከዚህም በኋላ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ 3ኛ ተከሳሽ ጋር በመገናኘት ዕፁንና ግለሰቡን 3ኛ ተከሳሽም በሚያሽከረክረው ኮድ 3_B 33259 አ.አ በሆነ “ቪትዝ” መኪና ውስጥ በማስገባት ግለሰቡ እንዲሸሽ ተደርጓል ሲል ዐቃቤ ሕግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በአራት ተከሳሾች ላይ ክስ አቅርቦ የነበረ ሲሆን÷ ከተከሳሾቹ መካከል በክስ መዝገቡ በ3ኛ ተከሳሽነት ተካቶ የነበረው ዳንዔል ተሥፋ የማነ የተባለ (ሹፌር) ተከሳሽን በሚመለከት በፖሊስ ተፈልጎ ባለመገኘቱና በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎለት ሳይቀርብ በመቅረቱ በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ክሱ እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን÷ 4ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ግን በሌለበት ጉዳዩ መታየት ቀጥሎ ነበር።

ሌሎቹ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባል የሆኑት 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ግን በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በተሰጠ ብይን መሰረት በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

በዚህ መልኩ ሁለቱ ተከሳሾች በቀረበባቸው የክስ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም በማለት የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ከሰባት በላይ የሰው ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ጉዳዩ በሌለበት የታየው የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የተባለ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበት ነበር።

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የዐቃቤ ህግ ማስረጃን አለማስተባበላቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፤ በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን፣ ያበረከቱትን የበጎ አድራጎት አስተዋጾን ጨምሮ እያንዳንዳቸው ያቀረቡትን አጠቃላይ ሰባት የቅጣት ማቅለያ አስተያየትን መያዙ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ ገልጿል።

በዚህም በዕርከን 20 መሰረት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በሌለበት ጉዳዩ የታየውን 4ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመቅረቡን ተከትሎ አንድ ማቅለያ በመያዝ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን 4ኛ ተከሳሽን በተገኘበት አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.