Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ ከቤልጂየም የልማት ትብብር ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቤልጂየም የልማት ትብብር ሚኒስትር ካሮሊን ጄኔዝ ጋር ዛሬ በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በውይይታቸው ላይም ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ያደነቁት አቶ ደመቀ÷ ቤልጂየም የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በመሆኗም እንኳን ደስአለዎት ብለዋል፡፡

የሁለትዮሽ ግንኙነትና የልማት ትብብርን በትምህርት፣ በጤና እና በሰው ኃይል ልማት ዘርፎች ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ስለ ሀገራዊ ምክክሩ፣ የሽግግር የፍትሕ ሂደት እንዲሁም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ላይ የመንግስትን ቁርጠኝነት አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም በውይይታቸው ስለ አየር ንብረት ተጽዕኖዎች ያነሱ ሲሆን÷ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉትን ጥረቶች ጠቅሰው የተቀናጀ ርብርብ እንደሚስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ከቀጣናዊ ጉዳዮች አኳያም ኢትዮጵያ የጋራ ደኅንነትና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትብብርን ለማረጋገጥ እንደምትሠራ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ካሮሊን ጄኔዝ በበኩላቸው÷ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የቤልጂየም መንግስትም ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.