አየር መንገዱ ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ተስማማ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ 20 ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና የቦይንግ ከፍተኛ የንግድ እና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ብራድ ማክሙለር ተፈራርመዋል።
አቶ መስፍን ጣሰው አውሮፕላኑ አሁን ካሉት አውሮፕላኖች ግዙፉ መሆኑን ገልጸው÷ አውሮፕላኑን ለመግዛት በማዘዝም ከአፍሪካ ቀዳሚው የኢትዮጵያ አየርመንገድ መሆኑን አስታውቀዋል።
አውሮፕላኑ 50 የቢዝነስ እና 390 የኢኮኖሚ በአጠቃላይ 440 መቀመጫዎች እንዳሉትም ገልጸዋል፡፡
ይህም ከፍተኛ ፍላጎት ያለባቸውን እንደ ዋሽንግተን እና ጓንዡ ያሉ የበረራ መደረሻዎችን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል እንደሆነም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ 65 ቶን የመሸከም አቅም እንዳለው የተነገረ ሲሆን÷ 71 ሜትር ርዝመት ያለው የአውሮፕላኑ ክንፍ መታጠፍ እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡
አውሮፕላኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ ያደረገው በፈረንጆች አቆጣጠር 2020 ሲሆን÷ ለንግድ አየር መንገዶች ግን የሚደርሰው በ2025 እንደሆነ ታውቋል።
በስምምነቱ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2027 ጀምሮ እስከ 2030 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 8 አውሮፕላኖችን ለመረከብ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።
አውሮፕላኑን ካዘዙት አየር መንገዶች መካከል ቀዳሚው ኤምሬትስ ሲሆን÷ 205 777X-9 አውሮፕላኖችን አዟል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ የገዛቸው አውሮፕላኖች 104 መድረሳቸው ተመላክቷል፡፡
በዘመን በየነ